በአጠቃላይ ፪ኛ ደረጃ የአማርኛ መማሪያ መጻሕፍት የአንብቦ መረዳት ክሂሎችና የንባብ አይነቶች ውክልና (`Amharic textbooks reading comprehension exercises in Secondary schools’)

Main Article Content

Agegnehu Tesfa

Abstract

መጽሐፎች የቀረቡ የቅድመ ንባብ፣የንባብ ጊዜና የድህረ ንባብ መልመጃች(ጥያቄዎች) የተለያዩ አንብቦ የመረዳት ንዑሳን ክሂሎችን ለማስተማር ያላቸውን ምጥጥን፣ ለከፍተኛ ደረጃ አንብቦ የመረዳት ንዑሳን ክሂሎች የሚሰጡትን ትኩረትና ሁለቱ የንባብ አይነቶች (ጥልቅና ሰፊ ንባብ ) ተገቢ ወክልና ማግኘት አለማግኘታቸውን መፈተሽ ነው። የጥናቱ ንድፍ ገላጭ ሲሆን ስልቱ ገምጋሚ ነው። ለዚህም በመረጃ ምንጭነት ያገለገሉት የዘጠነኛና የአስረኛ ክፍል የአማርኛ መማሪያ መጽሐፎች ናቸው። በእነዚህ ሰነዶች ላይ በተካሄደው ምርመራ መሰረትም በመጽሐፎቹ መልመጃዎች በቅድመ ንባብ፣ በንባብ ጊዜና በድህረ ንባብ ተግባራት ውስጥ 425 ጥያቄች አንብቦ የመረዳት ንዑሳን ክሂሎችን ለማስተማር እንደተዘጋጁ ማረጋገጥ ተችሏል። እነዚህ ጥያቄዎች የሚወክሏቸውን ክሂሎች ለማጥናትም ከተመራማሪው በተጨማሪ በሦስት ባለሙያዎች /በቋንቋ መምህራን ከተዛማጅ ድርሳናት ተጨምቀው በተወሰዱ 20 የአንብቦ መረዳት ንዑሳን ክሂሎች ስር ተመድበዋል። ከዚያም የተመደቡት ጥያቄች የሚወክሏቸው ክሂሎች በሰንጠረዦች እየቀረቡ በገላጭ ስታትሲቲክስ በተለይም በድግግሞሽና በመቶኛ ተተንትነው ተተርጉመዋል። የውጤት ትንተናውና ማብራሪያው እንዳመለከተውም በክለሳ ድርሳናት ክፍል ከተገለጹት መለኪያዎች አንጻር ሲመረመሩ አንደኛ በአንብቦ መረዳት ክሂልነት ከሚታወቁትና በ፪ኛ ደረጃ ትምህርትነት ሊቀርቡ ከሚገባቸው መካከል ተካተው የተገኙት የተወሰኑት ብቻ ናቸው። አብዛኛዎቹንና በሀገሪቱ ሥርዓተ ትምህርትና የሥርዓተ ትምህርት ማዕቀፍ እንዲሁም በክለሳ ድርሳናት ክፍል በተጠቀሱት ምሁራን በጣም አስፈላጊ የሚባሉትን ንዑሳን ክሂሎች ለማዳበር የሚያግዙ ጥያቄዎች በመልመጃዎቹ ውስጥ መካተት ሳይችሉ ቀርተዋል። ይህም በመጽሐፎቹ የተሸፈኑት አንብቦ የመረዳት ክሂሎች የውክልና ደረጃ ምጥጥን ችግር ያለበት እንደሆነ /በብዙ ጥያቄዎች ሊወከሉ የሚገባቸው በውስን ጥያቄዎች፣ በአንጻሩም በመመዘኛዎቹ መሰረት በዚህ ደረጃ በውስን/ጥቂት ጥያቄዎች ሊወከሉ የሚገባቸው በብዙ ጥያቄዎች እንዲወከሉ እንደተደረገ የውጤት ትንተናው አሳይቷል። ሁለተኛውን የምርምር ጥያቄ በሚመለከትም፣ዝቅተኛ ደረጃ አንብቦ የመረዳት ክሂሎች የሚባሉት (ለምሳሌ፣ በአሰሳ ንባብ መረጃን መፈለግ፣ ዝርዝር ሀሳቦችን መረዳት፣ለቃላትና ሀረጋት ዐውዳዊ ፍች መስጠት) ከፍተኛ ትኩረት የተሰጣቸው መሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል። በተቃራኒው አንብቦ የመረዳት ክሂሎችን በሚያነሱ ተዛማጅ ድርሳናትና በሀገሪቱ የትምህርት ፖሊሲና የፖሊሲው ማስተግበሪያ ማዕቀፍ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጣቸው ከፍተኛ ደረጃ አንብቦ የመረዳት ክሂሎች የሚባሉትን የዘይቤያዊ አገላለጾች ፍች ከገቡበት ዐውድ መረዳት፣በጽሑፍ ውስጥ በግልጽ ያልቀረቡ ሀሳቦችንና መረጃዎችን መረዳት(inference)፣መተንተን፣ማቀናበር፣ማዛመድና መገምገም የሚባሉት በመጽሐፎቹ ዝግጅት ችላ እንደተባሉ የጥናቱ ውጤት አመላክቷል። ሦስተኛ፣ በመማሪያ መጽሐፎቹ ጥልቅ (intensive) እና ሰፊ (extensive) የንባብ አይነቶች ያገኙት ትኩረት ሲመረመርም ሰፊ የሚባለው የንባብ አይነት ትኩረት እንዳልተሰጠው ብቻ ሳይሆን ጭራሽ እንደተዘነጋ ለማረጋገጥ ተችሏል። በአጠቃላይ በሦስቱም ጉዳዮች ላይ የተካሄደው የውጤት ትንተና የመማሪያ መጽሐፎቹ የአንብቦ መረዳት ክሂሎች ጥያቄዎች አዘገጃጀት በተዛማጅ ድርሳናት ክለሳ የቀረበውን የክሂሎች አቀራራብ የሚጻረር እንደሆነ አመላክቷል። ከእነዚህ የጥናቱ ግኝቶች በመነሳትም ወደፊት መጽሐፎቹ ሲሻሻሉ ሊደረጉ የሚገባቸው ጥንቃቄዎች እንዲሁም መምህራን ምን ቢያደርጉ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የሚታዩትን ክፍተቶች ሊሞሉ እንደሚችሉ የሚያመላክቱ የመፍትሄ ሀሳቦች ተጠቁመዋል።

Article Details

Section
Articles