የኢትዮጵያ አጠቃላይ ፪ኛ ደረጃ ትምህርት የአማርኛ ቋንቋ ማጠናቀቂያ ፈተናዎች ግምገማ በብሉም አዕምሯዊ ምድብ የትምህርት ዓላማዎች መነሻነት እና ፈተናዎቹ በመማር-ማስተማር ሂደቶች ላይ ሊያሳድሩት የሚችሉት ተጽዕኖ ::

Main Article Content

Agegnew Tesfaye

Abstract

የዚህ ጥናት ዋና ዓላማ የኢትዮጵያ አጠቃላይ ፪ኛ ደረጃ ትምህርት የአማርኛ ቋንቋ ማጠናቀቂያ ፈተና ከአዕምሯዊ ምድብ የትምህርት ዓላማዎች ጋር ያለውን ተጣጥሞሽ/ ተዛምዶ፣ የተዛምዶ ደረጃና በማስተማር-መማር ሄደቶች ላይ ሊያሳድረው የሚችለውን ተጽዕኖ መፈተሸ ነው፡፡ ይህን መሰረታዊ ዓላማ ለማሳካትም የሦስት ዓመታት የማጠናቀቂያ ፈተናዎች 270 ጥያቄዎች በዌር እና ሌሎች (1990)፣ ኦልደርሰንና ሌሎች(1995)፣ ችዱ (2010) እና ታንግስኩል (2017)ዓ.ም ስራ በተመለከተው የማዛመጃ ዘዴ መሰረት ከአዕምሯዊ ምድብ የትምህርት ዓላማዎች ጋር በማዛመድ ተገምግመዋል፡፡ የፈተናዎቹን ጥያቄዎች ከአዕምሯዊ ምድብ የትምህርት ዓላማዎች ጋር በማዛመድ የተሳተፉት ባለሙያዎችም አራት ሲሆኑ ሁለቱ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በሥርዓተ ትምህርትና ማስተማር፣ አንዱ በትምህርታዊ ሥነ-ልቦናና በምዘናና ግምገማ አንዱ አማርኛን በማስተማር የሰሩ የኮሌጅ መምህራን ናቸው፡፡ ተጨማሪ መረጃዎች ከፈተናዎች ኤጀንሲ ኃላፊዎችና የአማርኛ ቋንቋ ፈተና ዝግጅት ባለሙያዎች በቃለ መጠይቅ ተሰብስበው ተተንትነዋል፡፡ በተለይ በባለሙያዎቹ የተካሄደው ምደባ ውጤት ትንተና እንዳሳየውም፣ የፈተናዎቹ ጥያቄዎች ከአዕምሯዊ ምድብ የትምህርት ዓላማዎች ጋ ያላቸው ዝምድና አሉታዊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ይኸውም አንደኛ በፈተናዎቹ መወከል ያላባቸው ዓላማዎች ሁሉ አልተወከሉም፣ የተወከሉት ውክልናም ተጠየቃዊ/ሎጅካል ሆኖ አልተገኘም፡፡ ሁለተኛ በብዙ ጥያቄ ሊወከሉ የሚገባቸው ዋነኛዎቹ የትምህርቱ ጉዳዮች (ትግበራ፣ትንተና፣ ቅንበራና ግምገማ) በፈተናዎቹ እየተወከሉ ያሉት ከ10% በሚያንሱ ጥያቄዎች ብቻ እንደሆነ የጥናቱ ውጤት አሳይቷል፡፡ በአንጻሩም በትምህርት ፖሊሲ ሰነዶች ትኩረት ያልተሰጣቸው (ሊሰጣቸውም የማይገባቸው) እውቀት ማስታወስና ግንዛቤ/መረዳት ከ90% በላይ በሚሆኑ ጥያቄዎች የመወከል እድል እንዳገኙ የጥናቱ ውጤት አሳይቷል፡፡ ይህም ተማሪዎች በመማሪያ መጽሐፎቻቸው የቀረቡ መተግበርን፣ መተንተንን፣ ማቀናበርንና መገምገምን የሚጠይቁ የክሂል ትምህርቶችን ተግባራዊ የማድረግ ፍላጎት እንዳይኖራቸው የሚያደርግ በመማርማስተማር ሂደቶች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችል ነው፡፡ በተለይ ከክሂሎች ጋር የተያያዙ ከፍተኛ የማሰብ ችሎታዎችን የሚፈልጉ በተግባር እንዲጽፉ፣ እንዲወያዩ፣ እንዲከራከሩ፣ ንግግር እንዲያደርጉ ወዘተ. የሚያዙትን መልመጃዎች ፈቃደኛ ሆነው እንዳይሰሩ የሚያበረታታ ነው፡፡ የዚህም አንድምታ የፈተናዎች ኤጀንሲ አንደኛ፣ የሚመርጣቸው ጥያቄ አውጭዎች/ ጸሐፊዎች እነዚህን ዓላማዎች ያገናዘቡ ጥያቄዎች የማውጣት/ የመጻፍ አቅም/ ክሂል የላቸውም፤ ሁለተኛ፣ በኤጀንሲው ለየትምህርት ዓይነቶቹ ፈተና ዝግጅት ባለሙያዎች በተደጋጋሚ እየተሰጠ ያለው የፈተና አዘገጃጀት አቅም ማጎልበቻ ስልጠና በባለሙያዎቹ ላይ የሚፈለገውን ለውጥ አስገኝቶ ፈተና አዘጋጆቹ (ጥያቄ ጸሐፊዎች) የሚያወጧቸው ጥያቄዎች፣ እነዚህን ዓላማዎች በፖሊሲውና በቋንቋው ትምህርት በተሰጣቸው ትኩረት መሰረት የሚወከሉበትን አቅጣጫ ማሳየት አላስቻላቸውም የሚል ነው፡፡ ከጥናቱ ግኝቶች በመነሳትም የሚከተሉት አስተያየቶች ተሰጥተዋል፤ አንደኛ. የፈተና አዘጋጆችና ባለሙዎች መምረጫ መስፈርቶች ተገቢ ባለሙያዎችን መምረጥ የሚያስችሉ ተደርገው ቢዘጋጁ/ ቢከለሱ፣ ሁለተኛ. የሚዘጋጁት ፈተናዎች ከትምህርቱ ጋር የሚጣጣሙ እንዲሆኑ ማድረግ የሚያስችሉ ትምህርቶችና ስልጠናዎች ለፈተና አዘጋጆችና የፈተና ዝግጅት ባለሙያዎች የሚሰጥበትን መንገድ ማመቻቸት ቢቻል፡፡ ሦስተኛ፣ ለችግሮቹ መከሰት አንዱ መንስኤ ፈተናው በምርጫ ብቻ የሚቀርብ በመሆኑና በምርጫ ፈተና ከፍተኛ ደረጃ የአዕምሯዊ ችሎታዎችን መጠየቅ የተለየ ልምድንና ችሎታን ሊጠይቅ ስለሚችል በብዙ ሀገሮች እየተደረገ እንዳለው የሚዘጋጁት ፈተናዎች ምርጫ ብቻ የማይሆኑበት ሥርኣት ቢዘረጋ፡፡

Article Details

Section
Articles