የተክሌ አቋቋም ቃላዊ ታሪክ እና ፋይዳው

Authors

  • አዲሴ ያለው መንግስቱ

Keywords:

ባህላዊ ትምህርት ቤት፣ ተክሌ አቋቋም

Abstract

ይህ ጥናት የተክሌ አቋቋም ቃላዊ ታረክ እና ፋይዳው በሚል ርዕስ የቀረበ ነው። በዚህ መሰረት የተክሌ አቋቋም እንዴት እንደተደረሰ፣ ከትውልድ ትውልድ እንዴት እንደተላለፈ፣ በዘመናት ሂደት ውስጥ ታሪኩ ምን እንደሚመስል፤ አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ እና የተክሌ አቋቋም ትምህርቱን ጠቀሜታ ማሳየት የጥናቱ አላማ ነው። ይህን ከግብ ለማድረስ አላማ ተኮር እና እድል ሰጭ ናሙናን በመጠቀም በምልከታ፣ በቃለ መጠይቅ፣ እንዲሁም ከተለያዩ ሰነዶች የተሰበሰቡ መረጃዎች ከዓይነታዊ መረጃ መተንተኛ መንገዶች ውስጥ በገላጭና ትረካዊ ስልት ተተንትነዋል። በዚህ ጥናት የተገኘው ውጤት የተክሌ አቋቋም ባህላዊ ትምህርት በአለቃ ገብረ ሐና በጣና ሐይቅ አካባቢ እንደተደረሰ፤ ልጃቸውን ተክሌ ገብረ ሐናንም እንዳስተማሩ፣ ተክሌም ከአባቱ ያገኘውን ፈጠራ ይዞ ወሎ እንደሄደ፤ በወሎ ተንታ ሚካኤል ሲመረቅም አቋቋሙን እንዳቀረበው፤ ሊቅነቱ ከታወቀ በኋላ ንጉሥ ራስ ጉግሳ ወሌ ከወሎው ንጉሥ ራስ ሚካኤል አስፈቅደው ደብረታቦር ኢየሱስ እንዳመጡት ጥናቱ አሳይቷል። ራስ ጉግሳ ለተክሌ የቤተክርስቲያን አስተዳዳሪነትና መሪጌትነት (ተክሌ አቋቋምን የማስተማር ሀላፊነት) አንድ ላይ እንደሰጡት፤ ተክሌም አስከ እለተ ሞቱ ድረስ በደብረ ታቦር ኢየሱስ እንዳስተማረና ከእርሱ በኋላም የተለያዩ የተክሌ አቋቋም ሊቃውንት እያስተማሩ አሁን ካለው መምህር መርሻ መብራቱ አንዳደረሱት የጥናቱ ውጤት አመልክቷል። የተክሌ አቋቋም ክዋኔ በአሁኑ ወቅት በመጥፋት ላይ እንደሆነና ለዚህም ምክንያት የሆኑ ችግሮችን ጥናቱ አሳይቷል። ለእነዚህ ችግሮች መፍትሔ የሚሆኑ ሀሳቦች፡-የተክሌ አቋቋምን ይትበሀል (የማስተማር ሂደት) በመጽሐፍ በማሳተም የመማር ማስተማሩን ሂደት ምቹና ቀላል ማድረግ፤ የተክሌ አቋቋም ክዋኔውን በምስል (Documentary film) ቀርጾ ለሚቀጥለው ትውልድ ማስተላለፍ፤ በተለያዩ ባህላዊ ትምህርት ቤቶች ለተክሌ አቋቋም ምንጭ የሚሆኑ ትምርት ቤቶች ማቋቋም፤ የተማሪዎችን ፍላጎት ማሟላት እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት ለተክሌ አቋቋም አስፈላጊውን ትኩረት በመስጠት በቅርስነት መጠበቅ የሚሉትን ጥናቱ ጠቁሟል።

Downloads

Published

2019-11-19

How to Cite

አዲሴ ያለው መንግስቱ. (2019). የተክሌ አቋቋም ቃላዊ ታሪክ እና ፋይዳው. Ethiopian Renaissance Journal of Social Sciences and the Humanities, 6(1). Retrieved from https://erjssh.uog.edu.et/index.php/ERJSSH/article/view/119