እንስታዊነት በኢትዮጵያ ፍልስፍና፤ ሐተታ ዘርአ ያዕቆብና ሐተታ ወልደ ሕይወት እንደማሳያ

Main Article Content

Dawit Girma

Abstract

ይህ ጥናት በመካከለኛው የታሪክ ዘመን የተከሰቱትን ሁለት የኢትዮጵያ ፈላስፋዎችን ዘርአያዕቆብ እና ወልደሕይወት “ሴት”ን እንዴት
እንደተገነዘቧት ከእንስታዊ ሥነጽሑፋዊ ሂስ አንጻር ይመለከታል። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ መካከለኛው ዘመን “ወርቃማው የሥነጽሑፍ ዘመን”
በመባል ይታወቃል ። በዘመኑ ፋይዳ ብዙ ሀገር በቀልና ትርጉም የሥነሰብዕ እና የተፈጥሮ ሳይንስ ይዘት ያላቸው መጻሕፍት ተደርሰዋል ።
በመካከለኛው ዘመን ፍልስፍናዊ ይዘት ያላቸው እሳቤዎች፣ ቅኔዎችና መጻሕፍት ተጽፈዋል፤ ከፊል ኢትዮጵያዊ ሆነው ተወርሰዋል ። ጥናቱ
17ኛውን ክፍለዘመን የጊዜ ገደብ አርጎ በዘመኑ በምድረ እንፍራዝ፣ ጎንደር ይፈላሰፉ በነበሩ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ፈላስፋ ዘርአያዕቆብና
ደቀ መዝሙሩ ወልደሕይወት በጻፏቸው የፍልስፍና ድርሳናት/ሐተታዎች የሴትነትን ውክልና እንስታዊነትን (Feminism) እንደንድፈሃሳባዊ
መቀንበቢያ በመጠቀም በገላጭ ሥነዘዴ ሰነዶችን ተንትኗል ። የእንስታዊነት ንድፈሃሳቡም በሴቶች የማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አቅም
መጎልበትና እኩላዊ ሱታፌ ላይ አተኩሯል ። ሴቶች ዝቅ የሚደረጉባቸውን፣ የሚገለሉባቸውንና የሚበዘበዙባቸውን መንገዶች በመለየት ለመቃወም
ይሞክራሉ ። ይህን ጥናት ለማካሄድ ከአነሳሽ ምክንያቶች አንደኛው፣ በሀገራችን የነበረው የሴትነት አረዳድ ምን ይዞታና ታሪካዊ ዳራ እንዳለው
በሀገራችን ፈላስፎች አመክንዮ መሠረት ማየት ሲሆን፣ በተለይ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በአባዊ (Patriarchal) ሥርዓት ስር በነበረበትና
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየዳበረ ከመጣው እንስታዊ ንቅናቄ አስቀድሞ አሰላሳዮቹ ስለሴት ልጅ እኩልነት መርምረዋል ። ፈላስፋዎቹ በጋብቻ
ሕይወት፣ በንብረት መዝገብ፣ በአብሮነት ኑሮ፣ በስራ ክፍፍል፣ በጊዜ ሩካቤና በወር አበባ፣ አንድ ለአንድ ስለመወሰን አዎንታዊ እይታን
አንጸባርቀዋል ። ወልደሕይወትም ፍትሃዊ የነገረ ጾታ እሳቤው ከመምህሩ ጋር መሳ ለመሳ ቢሄድም ቅሉ፣ በተጻራሪው ሴትን ደካማና ስሜታዊ
በማድረግ ከብዙኃኑ አፍቃሬ ወንድ አቀንቃኞች ጋር በአንጻሩ ይዛመዳል ። ሴት ከወንድ እኩል መሆኗን ያብራራበት እሳቤው እንደመምህሩ
እስከመጨረሻው አብሮት አይዘልቅም ። በምዕራቡ ዓለም የኢትዮጵያውያኑ ፈላስፎች ዘመን ተጋሪ የሆኑ ፈላስፋዎችና አሳቢዎች በአባዊ ተጽዕኖ
ስር በወደቁበት ወቅት፣ አፍቃሬ ሴት ንቅናቄዎች ከመደርጀታቸው ምዕተ ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ጽሑፋዊ ፍልስፍና ለሴትነት ዋጋ ሰጥቶ
እንደነበር በሐተታ ዘርአ ያዕቆብና በሐተታ ወልደሕይወት ማሳያነት መደምደም ይቻላል ።

Article Details

Section
Articles